Monday, November 20, 2006

ቃልሽ ቃሌ ታምኖ

ብቻውን አንድ እንጨት አይሆንም ማገዶ፣
ቢረዳ ነው ልቤ መምጣቱ አንቺን ወድዶ፣
ወገግ ፍቅር ቢልለት ከፈጣሪ ማልዶ ፣
ሞላ ና ተርፈው የቃላት ማገዶ ፣
ተዓምር ሊሰራ ካንቺ ጋር ተጠምዶ ::

'ደሙሴ ቁጥቋጦ ፣
እሳቱ ተቀምጦ ፣
ፍቅሩን ካላየሁት፣
ምኑን ከምኑ ወደድኩት ፣
የማላውቀውን ሀገር -
አይደል የናፈኩት ?

ለመጣልን ከላይ ፣
ካልሆን ፍፁም አባይ፣
ይበሥላል ያ ፍቅር ፣
የተቸርነው ከግዜር፣
ምንም ቢመስል ጠጣር ::
እንዳይተንም ተኖ ፣
እንደሽቶ በኖ ፣
ደስታ ይዘምታል በሀገር -
ተላላፊ ሆኖ ::

በፍጡራን መሃል መልካም ማዛው ገኖ፣
በብዙ አፍቃሪ ቃልሽ ቃሌ ታምኖ፣
ሺህ ዘመን ይፃፋል ጥፍጥናውን ጭኖ፣
የመውደድ ማሳያ ደብዳቤንም ሆኖ ::

ቃላት ሥቀፈቅፍ ፍቅር ፍቅርን ወልዶ፣
ልቤ ሲፍለቀለቅ ምድጃ ተጥዶ ፣
ይንቀልቀል ከውጥሽ የማይጠፋው እሳት ፣
ፍቅር ከንቱ አይደለም የለም ቢሉም ሃሰት ::

No comments: