Monday, August 07, 2006

አንድ አይደለሁ እኔ

funny boxes? u need geez unicode.
you could read ande aydelehu ene > click here

በሃሳብ ከእሷ ጋር, ባካል ግን ከዚህ ነኝ
አንድ አይደለሁ እኔ, በሁለት አራቡኝ::

ሁለት ዕትብት አለኝ__
አንደኛው ተቆርጦ
ከልደት ቀዬዬ ድሮ የተቀበረ

ከእማምዬ ማህጸን__
ከአሪቲው ምድሯ
ተስማምቶ የቀረ::

ይሄኛው ዕትብቴ__
ቢሳብ የማያልቅ
የዚያኛው መንትያ

ላይን ተሰዋሪ_
ታስሮ ከማህጸኗ
ከማማዬ ኢትዮጵያ::

ምዕራብ ብሄድ ምስራቅ
ቢጎድል ብሞላ
ብቀል ወይ ብከብድ

የአዕምሮ ማሰሪያው__
የማህጸንዋ ቡንቧ
ጨርሶ አያስኬድ::

የወራት ተራራ_
እሙን አያስረሳ
በአመታት ቢለካ

ትዝታዋ ደወል_
ይመለሳል ከሷው
ሁን ላለው በረካ::

ናኘ ጥሪዋ __
ሲንቆረቆር በፍቅሯ አሸንዳ
ከዚህ ከዕምብርቴ

ተነሳብኝ ደግሞ__
ደምቃ አምራ ታየችኝ
ኢትዮጵያ እናቴ::

በሃሳብ ደረቴ ,አገር ቤት ነኝ ሥሳብ
አንድ አይደለሁ ስዎች , በሁለት ልታሰብ::

-//-


አምላኬ ሆይ !

የእምቧይ ካብ ነው ለካ
ልቤ አፈጣጠሩ፣
ለሺህ ተበተነ
ብትዋዥቅ ፍቅሩ ::

ካቻምና ተክቧል
ብትን ያለው ፈርሶ፣
በንፁህ ፍቅር ዘይት
እጅግ በጣም ርሶ ::

ሲሸራራፍ ወይኔ
ከውሥጤ ተሰማኝ፣
ተንዶ ሠላሜ
አንገቴን ሊያስደፋኝ፣

ኦ !
አቤቱ አምላኬ ሆይ !
ልቤን ጠብቅልኝ፣
ይብቃው ካንተ ወዲያ
ሰው አያምልክብኝ፣
የተራሮች ፅናት
ጉልበትን ስጥልኝ ::


-//-

ተዋኔው

ደፍሬ ጠየኩኝ
ዛሬስ ለተዋኔ፣
መልሥ ዞሬ ባጣ
ግራ ሆኖብኝ ለእኔ ::

"ያውጡኝ ባክዎ ከማጥ
ብልህ ኖት አውቃለሁ፣
ቸር ሰው ጅል ሲባል
በአያሌው ሰማለሁ ::

ሠጥቶ ካለችው ላይ
አለሁልህ ያለ፣
በዋለው ውለታ
ስንቱ ሰው ቀለለ ::

ዕውነት ሞኝነት ነው
መልካም ማድረግ ለሰው፣
እባክዎን ተዋኔ
መልሶን እስቲ ልስማው ::"

ተዋኔው __
የአገጫቸውን ሪዝ
ያዝ _ለቀቅ አርገው፣
አንዳች አማልዕክት ም
ጠያቂ ሰው መስለው፣
እያዩ አሻቅበው
ከሰማይ ሰማዩ፣
አይኖቻቸው በርተው
ጥርሶቻቸው ታዩ ::

"ዶሮይቱ ዕንቁላልን
ብትጥል ባትጥል፣
ትታረድ የለም ወይ
አንት ጎበዝ አስተውል ::

የወይን ሃረግ ግንዱ
ያ ፍሬ ዠርጋጋ፣
ሰው ይሄድ የለም ወይ
ፍሬው ፍለጋ፣
ጥላውን ሊጠጋ፣
አስተውል አይጥበብህ
ልጄ ተረጋጋ ::

የዕባብ ዕንቁላልን
ማነው የፈለገ ?
የመርዝ ፍሬያትን
ማነው እሱ ያፈፈ ?
ዕድሜውን ቆጥሮ
ራሱ ካልረገፈ፣
ማን ሊኖር ለሱ የከነፈ ::

ደግ ሰው እንዲያው ነው
ጣፋጭ ፍሬ ያዘለ፣
የሚኖር ለሌሎች
ምርጡን ዕያደለ ::
መልዕክተ ነፍሱን
ሰጪ ሰውነው ያ ሰው፣
ከሰማይ ሲልከው፣
ሲያበጃጅ ሲሰራው ::"

አሉና .............
ትንሽ ዝም እንዳሉ፣
ልቤ ወተወተኝ
እንደወትሮ አመሉ ::

አኔም __
አሰብኩ መከርኩኝ መከረኩኝ
ደግሜ ደግሜ፣
እምቢ አልኩኝ ለክፋት
መርዝ እንዳይሆን ደሜ ::

የኔው ከእኔው ጋር
ሙግቴን ተረድተው፣
"የመስዋዕቱ ጭስ "
በማለት ቀጠሉ ተዋኔው፣
"ከሰማየ ሰማያት
አልፎ የሚዘልቀው ፣
ጆሮ እንዳለህ ስማኝ
መልካም ሰው የእግዜር ነው ::"

-//-


መቶ ሀያ ሺ ሻማ


ጨልሞበት ኑሮ
አዱኛ ሳያጣ፣

እንደቀድሞው አዳም
ሔይዋን ሳትመጣ፣

በብቸኛ ግዞት
ተቆጣ ! ተቀጣ !

ሥትመጣለት በራ
ከመቶ ሀያ ሺ ሻማ፣

ጠራ መላ አካሉ
እንደመልአክ ሸማ ፣

ሔይዋኑ ለኩሳው
በ ' የኔ ቆንጆ ' ዜማ ::
-//-

መች ባርነት ቀረ ?!

ሰው ሰውን ገዝቶ
እንደሰው ሳይቆጥር፣
እንደቤት እንስሳ
ሰው ይነዳ ነበር ::
አሳዳሪው ጌታ
ባሪያም የነበረ፣
ዘመን ተለውጦ
ባሪያም ጌታ ቀረ ::

ቀረ ልበለ እስቲ
የሆዴን አምቄ፣
በየጎጆው እንዳለ
ጠንቅቄ አውቄ ::
ተሰወረ እንጂ ካይን
መች ባርነት ቀረ፣
ማነው ተበድሮ
በሰላም የዋለ በሰላም ያደረ ?

ያማረ መኪና
ዛሬ ባሽከረክር፣
ትዳርን መስርቼ
ሦስት ጉልቾች ባኖር ::
ታፍኜ እስክሞት ነው
በብድር ላይ ብድር፣
እንዳይፈርስ ውጥኔ
ቀን ከ ለሊት ስበር ::

በአበዳሪ ብዛት
እጅግ ተራኩቼ፣
ለነዚህ ቱጃሮች
የኑሮ ጌቶቼ፣
ሰርቼ ገፍቼ
ሞቼ ተሟሙቼ፣
እንካችሁ እላለሁ
በዕዳ ላይ ዕዳ፣
የዕድሜ ይገላግልህ ባርነት ገብቼ ::

No comments: